Skip to content
Home » ስመኝ

ስመኝ

ስመኝ በላይ ትባላለች፡- የመጣችው ከአማራ ክልል ሲሆን የተወለደችውም ከድሃ ቤተሰብ ነው ፡፡ ስመኝ ህይወቷን ቀይራ ቤተሰቧን ለመርዳት አስባ በጉልበት ሥራ ወይም በቤት ሰራተኛነት ሥራ ለመቀጠርና ገቢ ለማግኘት ተስፋ በማድረግ አዲስ አበባ ገባች፡፡ ከዚያ መጀመሪያ የቤት ሰራተኛ ሆና መሥራት ጀመረች ፡፡ በዚያን ጊዜ ነበር ከበእምነት አባት ጋር ግንኙነት ጀመረች፡፡ የመጀመሪያ ልጇን ህፃን በእምነትን ወልዳ ከ7 ዓመታት በኋላ ደግሞ ሁለተኛ ልጇን ፀነሰች፡፡ ከዚህ በኋላ ነበር ያላሰበችው ነገር የገጠማት ባለቤቷ ከ 7 ዓመት ሴት ልጇ ከበእምነት ጋር እና በሆዷ ከያዘችው ፅንስ ጋር ብቻዋን ትቷት ሄደ፡፡ ስመኝ እራሷን ለመርዳት ያገኘችውን ማንኛውንም ነገር ለመስራት ሞከረች ነገር ግን ከልጅዋ ጋር እሷን ለመቀጠር ፈቃደኛ የሆነ ማንም የለም ፡፡ ልጇን ሱራፌልን በወለደችበት ወቅት ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ ችግሩ ጠናባት፡፡ ያለ ሥራ ያለሰው ድጋፍ በምንና እንዴት መኖር ይቻላል እሷም ልጆቿም የሚበሉት እስኪያጡ ተራቡ፡፡ ቤት አልባ እና ተስፋ የቆረጠች ሆና ከልጆ በእምነት እና ከህፃን ሱራፌል ›ጋር ለመኖር ወደ ልመና ለመሄድ ተገደደች ፡፡

ወቅቱ ፍቅር ለሕጻናትና ለእናቶች በጎ አድራጎት ድርጅት ሊመሠረት በሂደት ላይ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ የፍቅር በጎ አድራጊዎቹ በየመንገዱ ላይ የተቀመጡ ለጆች የያዙ እናቶችን እያነጋገሩ ሲመጡ ስመኝ ከበእምነትና ከጨቅላ ሕፃን ሱራፌል ጋር በመንገድ ላይ እርዳታ በመጠየቅ ተቀምጠው ነበር፡፡ ከፍቅር በቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት ልጆች በሕፃናት መዋያ ቢውሉ ሠርቶ ለመብላትና ለመለወጥ ዝግጁ ነሽ ወይ የሚል ጥያቄ ስትጠየቅ እውነት መሆኑን ከልቧ ባትቀበለውም አዎን ልጄ ከተያዘ ሠርቼ ከዚህ አስከፊ ልመና ሕይወት ወጥቼ ሠርቼ መለወጥ በጣም እፈልጋለሁ፡፡ በማለት መለሰች ጭላንጭል ተስፋ ያየች ያህል ደስ እያላት ፡፡ ሴቷ ልጄ ትምህርት ቤት ስለገባች ሕፃኑ ከተያዘልኝ ምንም አይከብደኝም በማለት አከለች፡፡ ብዙዎች የሚጠይቁትን ጥያቄ እሷም ጥሪ ላደረጉላት የፍቅር መስራቾች ጠየቀች፡፡ ግን ‹‹የምትሉን እወነት ነው ወይስ ሌሎች ልባችንን አድርቀውን እንደሚሄዱት ሰዎች ናችሁ?›› ብላ ጠየቀች ሁሉ ነገር ጭልም ስላለባት ምንም በጎ ነገር የሚታያት ሰው አልነበረችም ሕይወት አታክታታለች፡፡ ግድየለም በቅርቡ መጥተን የተናገርነውን በተግባር እናሳያችኋለን በማለት ቃል ገብተው የሄዱት፡፡ ከጥቂት ቀን በኋላ ፍቅር ለህፃናት እና ለእናቶች በጎ አድራጎት ድርጅት የተመሠረለትን ዓላማ ዕውን ለማድረግ ቆርጦ በመነሳት ህልም የመሰለውን የእነስመኝ ዓይነት ችግረኛ ማንሳት የጀመረው፡፡

በዚህ ጊዜ ነበር ፍቅር ለህፃናት እና ለእናቶች በጎ አድራጎት ለስመኝና ለልጆቿ የደረሰላቸው፡፡ ሙሉ እርዳታ ማግኘት ጀመሩ፡ ከሚያገኙትም አገልግልቶች በቀን ሦስት ጊዜ ትኩስና ተመጣጣኝ ምግብ ፣ ንፅህናቸው ይጠበቃል፣ የልብስና የጫማ ስጦታ ያገኛሉ፤ ቢያማቸው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋሉ፡፡ ሁሉንም በፍቅር ውስጥ በነፃ እያገኙ ቀጥለዋል፡፡ ትልቋ ልጇ በእምነትም የሚያስፈልጋትን የትምህርት ቁሳቁስና ልብስና ጫማ ተሰጥቷት የ1ኛ ክፍል ትምህርቷን ቀጥላለች፡፡ስመኝም ልዩ ልዩ የህይወት ክህሎተን ጨምሮ የሥራ ሥልጠና በመወሰድ የድርጅቱ የህፃናት ተንከባካቢ ሞግዚት ሆና ተቀጠረች፡፡ ይሄ ደግሞ ለልጇ ለሱራፌል እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ገና ጡት የሚጠባ ጨቅላ ሕፃን ስለሆነ ያለ ሀሳብ ሥራዋን እየሠራች ልጇንም ማጥባት ችላለች፡፡ በትርፍ ጊዜዋም የግለሰብ ቤት ውስጥ ሥራ እየሠራች ትገኛለች፡፡ አማካይ ወርሃዊ ገቢዋ 2200.00 ብር ሲሆን ይህም ለቤት ኪራይ እና ለወርሃዊ ፍጆታ በቂ ገቢ ነው ፡፡ አሁን ስመኝና እና ልጆቿ ከፊታቸው ብሩህና አስደሳች ሕይወት እንደሚጠብቃቸው ሙሉ ተስፋ አላቸው ፡፡

እነሱን ለመደገፍ ከእኛ ጋር ለቆማችሁ ሁሉ በእናቶችና በሕፃናት ስም እንዲሁም በፍቅር ስም ከልብ እናመሰግናለን!

እግዚአብሔር ዘመናችሁን ይባርክ!
ፍቅር የወደቁትን ያነሳል!
ፍቅር ለሕፃናት እና ለእናቶች በጎ አድራጎት ድርጅት

ለተጨማሪ መረጃ

አዳዲስ ዘናዎችን አና ሁነቶችን ለማኘት ይመዝግቡ !

We don’t spam!