Skip to content
Home » ፋንታዬ

ፋንታዬ

ፋንታዬ እዘዘው ትባላለች: የመጣችው ከአማራ ክልል ሲሆን ቤተሰቦቿም ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ የሚኖሩ ድሃ ገበሬዎች ናቸው ፡፡ ፋንታዬ በቀን ሰራተኛነት ወይም የቤት ሰራተኛነት ተቀጥራ በምታገኘው ገቢ ህይወቷን ቀይራ ቤተሰቧን ለመርዳት ተስፋ በማድረግ አዲስ አበባ ገባች ፡፡ ከዚያ በመጀመሪያ የቀናት እና ያገኘችው የቤት ሠራተኝነቱ ነበር፡፡ የቤት ሰራተኛ ሆና መሥራት ጀመረች ፡፡ ትንሽ ጊዜ እንደሠራች ይበልጥ ገቢዎን ለመጨመር አስባ የተሻለ ነው ወዳለችው የቀን ሥራ ገብታ ተቀጥራ መሥራት ቀጠለች፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ከልጆችዋ አባት ጋር ግንኙነት የጀመረችው ፡፡ በባህላዊ መንገድ ተጋብተው አብረው መኖር ጀምረው ሳለ መንትያ ልጆቿን አረገዘች፡፡

በዚህ ጊዜ ነበር የባለቤቷ ባህርይ መለዋወጥ የጀመረው በመጨረሻም የ5 ወር ነፍሰጡር ሆና ጥሏት ጠፋ፡፡ ትዳሬ ነው ያለችውን ሰው በድንገት አጥታ ያላሰበችውና ያልጠበቀችው ክፉ አጋጣሚ የደረሰባት ፋንታዬ ብታፈላልገውም ልታገኘው ስላልቻለች የሚገጥማትን ለመጋፈጥ ቆርጣ ተነሳች፡፡ ልጆቿን እስክትወልድ ድረስ ሥራዋን ጠንክራ በመሥራት ሳትቸገር አሳለፈች፡፡ ነገር ግን ከወለደች በኋላ እርሷንና መንትዮቹን የሚደግፍ ወይም የሚረዳት ሰው አልነበራትም፡፡ ሰው ካልሠራና ገቢ ከሌለው እንዴት መኖር ይችላል? ሠርታ ለመብላትስ ልጆቿን ምን ታድርጋቸው ፋንታዬ ከባድ ፈተና ውስጥ ወደቀች ቤት አልባ እና ተስፋ የቆረጠች በመሆኗ እሷና ልጆቿ በሕይወት ለመኖር የሚያስችላቸውን መላ ስታስብ ልጆቿን ይዛ በመንገድ ላይ በመቀመጥ መለመን አማራጭ የሌለው መንገድ እንደሆነ አሰበች፡፡ ‹‹የሀገሬ ሰው ራበኝ ብለው አይነሳኝም›› ብላ አሰበች፡፡ ስለዚህ ከልጆቿ ከቅዱስና መክሊት ጋር ’ጋር ወደ ጎዳና ለመሄድ ተገደደች ፡፡ በዚህ ሁኔታ ነው የጎዳናን ህይወት የተጋፈጠቸው፡፡

ፋንታዬ ሥራ ሠርታ እራሷን ችላ መኖር ህልሟ ነው፡፡ እንደ እናት ለልጆቿም የተመቻቸ ህይወት ናፍቆቷ ነው፡፡ ነገር ግን የሆነውን ከመቀበል በቀር ምንም ምርጫ አልነበራትም ፣ ምክንያቱም መንትዮች ልጆቿን ይዛ የትኛውንም ሥራ ለመሥራት አትችልም ለመቅጠርም ማንም ፈቃደኛ አልነበረም ፡፡ ይህንን የጎዳና ህይወት ህይወት አድርጋ በምታገኛት እርጥባን ለራሷና ለልጆቿ በማብላት ከመሰል ችግረኞች ጋር ብዙ ሆነው የሚያድሩበት ደሳሳ ቤት ውስጥ መኖር ቀጠለች መኖር ከተባለ!! የሰው እጅ እያዩ መኖር አንዴ ሲሞላ አንዴ ሲጎድል አንዴም ሲራቡ አንዴም ሲጠግቡ ሳትወድ የገባችበትን ህይወት ለሁለት ዓመታት በተስፋ ቢስነት ዘለቀ፡፡ለቅሶን እንጂ ሳቅን የማያውቁት እንቡጥ አበቦች የልጅነት ወዛቸው ጠፍቶ ፊታቸው በፀሐይና በአቧራ በልዞ ልብሳቸው ቆሽሾ፤ ከምግብ ማነስ የተነሳ ፀጉራቸወው ሳስቶና ቀልቶ ጉስቁል ብለዋል፡፡ ዓይኖቻቸው የተስፋ በማጣት ደስተኛነት እርቋቸው ይታያሉ፡፡

በዚህ ጊዜ ነበር ፍቅር ለህፃናት እና ለእናቶች በጎ አድራጎት ለፋንታዬና ለልጆቿ የደረሰላቸው፡፡ በተገኘው ክፍት የተጠቃሚ ቦታ ላይ የመምረጫ መስፈርቱን ሊያሟሉ ከሚችሉት የደሃ ደሃ እናቶችና ህፃናት ፋንታዬና ልጆቿ እድሉ ተሰጥቷቸው ወደ ፍቅር ዘለቁ፡፡ ፍቅር በፍቅር ተቀብሎ በፍቅር አቀፋቸው ቅዱስና መክሊትን ሁሉ ነገር ወደተሟላበት ምቾት ወዳለበት ወደ ፍቅር ሕፃናት መዋያ ሲገቡ ፋንታዬም ከስነልቦና እርዳታ ጀምሮ ከልዩ ልዩ የህይወት ክህሎት ሥልጠና በኋላ ወደ ናፈቀችው ሥራ ተሰማራች፡፡ ፋንታዬ ደስታዋ ወደር አልነበረውም ፡፡ ጠውልገው የነበሩት እንቡጦችም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለቅሶአቸው በሳቅ ተለውጦ ደስተኞችና ተጫዋቾች ሆኑ፡፡ የውብ አበቦቹ ፊት ብሩህ ሆኗል፡፡

አሁን ሕጻናቱ በፍቅር መዋእለ ሕጻናት ከጠዋት 2፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ቀኑ 11፡30 ድረስ ሙሉ እንክብካቤ እያገኙ ይገኛሉ፡፡ ከሚያገኙትም አገልግልቶች በቀን ሦስት ጊዜ ትኩስና ተመጣጣኝ ምግብ ፣ ንፅህናቸው ይጠበቃል፣ የልብስና የጫማ ስጦታ ያገኛሉ፤ ቢያማቸው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋሉ፡፡ ሁሉንም በፍቅር ውስጥ በነፃ እያገኙ ቀጥለዋል፡፡ ፋንታዬም በገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴ አንዱ በሆነው በመኪና እጥበት ላይ እየሰራች ነው ፡፡ በትርፍ ጊዜዋም የግለሰብ ቤት ውስጥ ሥራ እየሠራች ትገኛለች፡፡ አማካይ ወርሃዊ ገቢዋ 2500.00 ብር ሲሆን ይህም ለቤት ኪራይ እና ለወርሃዊ ፍጆታ በቂ ገቢ ነው ፡፡ አሁን ፋንታዬ እና ልጆቿ ከፊታቸው ብሩህና አስደሳች ሕይወት እንደሚጠብቃቸው ሙሉ ተስፋ አላቸው ፡፡

እነሱን ለመደገፍ ከእኛ ጋር ለቆማችሁ ሁሉ በእናቶችና በሕፃናት ስም እንዲሁም በፍቅር ስም ከልብ እናመሰግናለን!

እግዚአብሔር ዘመናችሁን ይባርክ!
ፍቅር የወደቁትን ያነሳል!
ፍቅር ለሕፃናት እና ለእናቶች በጎ አድራጎት ድርጅት

ለተጨማሪ መረጃ

አዳዲስ ዘናዎችን አና ሁነቶችን ለማኘት ይመዝግቡ !

We don’t spam!